ቀጥታ፡

የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ አማራጭ እየፈጠረ ነው

አሶሳ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ አማራጭ እየፈጠረ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የከተማዋ የኮሪደር ልማት አካል የሆነውን የአሶሳ ሲቲ ፓርክን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በርካታ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አብረው እንዲገነቡ አድርጓል።


 

ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ አማራጭ እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም የኮሪደር ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች በዘመናዊ መልኩ የተገነቡትን የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የሕጻናት መጨዋቻ እና የመዝናኛ ቦታዎች በማሳያነት ጠቅሰው፤ የልማት ሥራዎቹም ለትውልድ የሚተርፉ ናቸው ብለዋል።

አሶሳ ሲቲ ፓርክ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመሆኑ ባለፈ ሕፃናት አዕምሯቸው እንዲታደስ የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን አካቶ መገንባቱንም ተናግረዋል።


 

የክልሉ መንግስት በሌሎች አካባቢዎችም የኮሪደር ልማቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ በማከናወን ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ ከተሞችን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አብዱልከሪም አብዱራሂም በበኩላቸው፤ የአሶሳ ሲቲ ፓርክ የከተማዋን የመዝናኛ ማዕከል እጥረት ችግር የፈታና ለሕፃናትም ልዩ ስጦታ መሆኑ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም