ቀጥታ፡

የአረፋ በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችንና አቅመ ደካሞችን በማገዝ ሊሆን ይገባል

መሃል አምባ፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፡- የአረፋ በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችንና አቅመ ደካሞችን በማገዝ እንዲሁም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን በመደገፍ መሆን እንዳለበት የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ።

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል አንዱ ነው።


 

በብዛት የእርድ ሥነ ስርአት ተከናውኖበት የሚከበረው ይህ ታላቅ በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በመጠያየቅ፣ በአብሮነት፣ በመደጋገፍና ማዕድ በመጋራት ይከበራል።

በዚሁ መሰረትም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞንና አካባቢው ከሃይማኖታዊ መገለጫዎቹ ባለፈ የአንድነት እና የአብሮነት እሴቶቹን በጠበቀ መልኩ በጋራ ይከበራል።

በመሆኑም በዓሉ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝና በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን (የቲሞችን) ማዕድ በማጋራት፣ በማብላትና በማልበስ መሆን እንዳለበት የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አባስ ያሲን ገልጸዋል።

እለቱ ሲከበር መተሳሰብንና መረዳዳትን መሰረት አድርጎ መሆኑን አስረድተው በዚሁ መሰረት የዘንድሮውን የአረፋ በዓል ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።


 

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ፤ የአረፋ በዓል አከባበር የአብሮነት እሴት መገለጫና የመተሳሰብ ምልክት መሆኑን አንስተው በዓሉን በአብሮነት ማዕድ በማጋራትና በመተጋገዝ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የ1447ኛውን የአረፋ በዓል ምክንያት በማድረግ በዞኑ ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ጥላሞ ቀበሌ በተዘጋጀ ፌስቲቫል ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የጉራጌ እና የምስራቅ ጉራጌ ዞን አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም