ቀጥታ፡

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ እየዳበረ መምጣቱ የታየበት ነው

ጎንደር፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ እየዳበረ መምጣቱ የታየበት መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

ፓርቲዎች በሃሳብ የበላይነት ክርክር ያካሄዱበትና የዜጎች ሰፊ ተሳትፎ የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በርካታ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት ካርድ የያዙበትና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

በዚህ ታሪካዊ እለትም ዜጎች ድምፃቸውን በመስጠት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እለቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን እየተናገሩ ነው።

በምርጫ ሂደቱ አጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ሲል ኢዜአ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ምሁራንን አነጋግሯል።

ምሁራኑ በአስተያየታቸው ጠቅላላ ምርጫው የእስካሁኑ ሂደት የሃሳብና የፖሊሲ ክርክሮች የተካሄዱበት ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አንዳርጋቸው ተስፋሁን፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ እየዳበረ መምጣቱን ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫ ሂደት አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን አንስተው በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና አጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ ለዚህ ጥሩ መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በዩኒቨርሲቲው የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ክፍል የስትራቴጂና የወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት አስተባባሪ ሀቢብ ሰይድ ናቸው።

የምርጫ ሂደቱ እስካሁን በዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ በፓርቲዎች ጠንካራ የፖሊሲ ክርክሮች በሃሳብ የበላይነት መካሄዱን አንስተዋል።

በመሆኑም ሂደቱ በኢትዮጵያ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እውን እየሆነ መምጣቱን ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መገለጫ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ሂደቱ ፍትሃዊ፣ አካታች፣ ሰላማዊና ተአማኒ መሆን እንዳለበት አንስተው የእስካሁኑ ሂደትም ይህንኑ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የስነ ጽሁፍ መምህር የሆኑት ገብሬ ሙሉዓለም (ዶ/ር)፤ የምርጫ ሂደት የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ባህል የሚጎለብትበት፣ እድገትና ልማትን የሚወስን ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ጠቅላላ ምርጫው ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን አንስተው እስከ መጨረሻው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁላችንም ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዩኒቨሲቲው የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህርት የሺወርቅ ተዘራ፤ ምርጫ የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደትና የስልጡን ፖለቲካ መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም