ቀጥታ፡

ለህዝብ የገባነውን ቃል ለመፈፀም የማያቋርጡ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ ለህዝብ የገባነውን ቃል ለመፈፀምና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የማያቋርጡ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰባተኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት አዲስ ባለ 6 ወለል ህንፃ በመገንባትና በቴክኖሎጂ በማደራጀት ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አመልክተዋል።

ለዘመናት በተንዛዛ አሰራርና እጅ መንሻ እየተጠየቀበት ዜጎችን ሲያማርር የነበረውን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ስርነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት የመፍጠንና መፍጠር መርህ እየተከተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ፍትሃዊ ለማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አግልግሎት አንድ ብሎ መጀመሩን ነው ያነሱት።

ይህን ዲጂታል አገልግሎት ለማህበረሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ቀንና ሌሊት በከፍተኛ ትጋት ሲሰራ መቆየቱንም እንዲሁ።

በዚህም መሰረት ዛሬ ሰባተኛውን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ማዕከል ለአግልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ህዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በመሄድ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ በተንቀሳቃሽ የአዲስ መሶብ አገልግሎት ይበልጥ ወደ ህዝቡ እንዲጠጋ በማድረግም አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ነው ያብራሩት።

ለህዝብ የተገባውን ቃል ለመፈፀም እንዲሁም ብልጽግና እውን እንዲሆን ተከታታይነት ያለው የማያቋርጥ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ ህብረተሰቡ በሚቀርበው ማዕከል ያለምንም መንገላታት በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም