ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ የተተገበሩ ዲጂታል አሰራሮች አገልግሎት አሰጣጥን በተጨባጭ አሻሽለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ የተተገበሩ ዲጂታል አሰራሮች አገልግሎት አሰጣጥን በተጨባጭ አሻሽለዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ በተደረጉ ዲጂታል አሰራሮች አገልግሎት አሰጣጥን በተጨባጭ ማሻሻል መቻሉን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባው ከመዲናዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን፣ ሰባተኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል የዲጂታል አገልግሎት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍን መርቀው ወደ ስራ አስገብተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ እንዳሉት፤ በመዲናዋ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ዘላቂ እልባት ለመስጠት ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።
ለአብነትም ሁሉንም አገልግሎቶች በተቀናጀ መንገድ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል የዲጂታል አገልግሎትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት ማዳረስ ተችሏል ብለዋል።
ዛሬ ወደ አገልግሎት የገባውን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ ጨምሮ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ማለቱን ጠቅሰው፤ በማዕከላቱ የሚሰጡ የአገልግሎት አይነቶችም ወደ 150 ማደጋቸውን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የተገልጋዮች እርካታ 98 በመቶ መድረሱን ገልጸው፣ በቀጣይም ተጨማሪ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመዲናዋ በሌሎች የልማት መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ለመድገም ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዛሬ ወደ አገልግሎት የገባው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት መስጫ ማዕከል የዚህ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ፣ በማዕከላቱ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት በኩል በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ካባ መብራቱ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ወደ ስራ መግባቱ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ድልድይ ነው ብለዋል።