ቀጥታ፡

በኢሉአባቦር ዞን በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

መቱ፣ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ):- በኢሉአባቦር ዞን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብርናን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ። 

በዞኑ በክረምት እርሻ ከ389 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች የመሸፈን ስራም ተጀምሯል።

በክረምት እርሻው በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች የሰብል ዓይነቶች የሚዘሩ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም የሚታረስ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ ተናግረዋል።


 

ምርታማነትን ለማሳደግም በኩታ ገጠም የማረስ ልማድን በማዳበር እንዲሁም በማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በትኩረት መሰራቱን ኃላፊው ገልጸዋል። 

ለዚህም ከ161 ሺህ ኩንታል በላይ የኬሚካል ማዳበሪያ እና ከ24 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች በክረምት እርሻው በስራ ላይ እንደሚውሉ አስታውቀዋል። 

ከዚህ ውስጥ 61 ሺህ ሔክታር መሬት በበቆሎ ሰብል የሚሸፈን ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር የሚሆን ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ መቅረቡንም አክለው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በዞኑ ስር በሚገኘው የያዮ ወረዳ በክረምት እርሻ ከ11 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች የመሸፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በፈቃዱ ኦልጂራ ገልጸዋል። 

በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን በማስፋፋትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮችም በኩታ ገጠም በማረስ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናቸውንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ለክረምት እርሻው ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በያዮ ወረዳ የአጪቦ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጌታቸው በቀለ፣ አርሶ አደር ተስፋዬ ሀብተማርያም እና አርሶ አደር ብርሃኔ አሰፋ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ከ116 ሔክታር በላይ መሬት ላይ በቆሎ መዝራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ የማሳ ዝግጅት ስራቸውን ቀደም ብለው በማከናወናቸው እንዲሁም የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦትም ቀድሞ በመድረሱ ማሳቸውን በዘር የመሸፈን ተግባርን ቀድመው መጀመራቸውን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም የግብርና ስራቸውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በትራክተር የማረስ ስራ እንዲያከናውኑ በወረዳው አስተዳደር በኩል አስፈላጊው እገዛ እንደተደረገላቸውም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም