በወረዳው የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከእንግልት ታድጎናል - የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በወረዳው የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከእንግልት ታድጎናል - የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች
አሶሳ፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦ በወረዳው የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለውሃ ፍለጋ ከሚያደርጉት ረጅም ጉዞ እንደታደጋቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንጌ ወረዳ በሚገኙት ቁዱዩ እና ቱመት ጀበሮና ቀበሌዎች፣ የፋሮ ፋውንደሽን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ለአገልግሎት አብቅቷል።
ይህም ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በወቅቱ ተገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የተገነባላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ለውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት በመጓዝ ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት የሚታደግላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ከቀበሌው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሰሚራ ሀሚድ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ ለመቅዳት ረጅም ሰዓታትን በእግር ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን በቀበሌያቸው የተገነባላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ችግሩን በመቅረፍ በአካባቢያቸው የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ መሆን ስላስቻላቸው ይደርስባቸው ከነበረው ድካም እፎይታ አግኝተዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ አብዱሰላም ራህማ በበኩላቸው፤ በቀበሌያቸው የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃቱ የበርካታ ዓመታት የሕዝብ ጥያቄን የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ለጤናቸውም ሆነ ለማኅበራዊ እለታዊ ተግባራቸው የሚሆን ንፁህ መጠጥ ውሃ ማግኘት መቻላቸው፣ በውስጣቸው ልዩ ደስታና እርካታን እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ለረጅም ዘመናት አገልግሎት መስጠት እንዲችል፤ ከእንስሳት ንክኪም ሆነ ከማንኛውም ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች በመጠበቅ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ መልሃሴን ሱልጣን በበኩላቸው፤ የውሃ እጦቱ በተማሪዎች ላይ ያደርስ የነበረውን ተፅዕኖ ሲያብራሩ፣ ልጆችም ውሃ ለመቅዳት ረጅም ርቀት ለመጓዝ በመገደዳቸው ምክንያት መደበኛ ትምህርታቸው ያመልጣቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በመንጌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ መለስ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የኅብረተሰቡን የውሃ እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ፣ ሆስፒታሉ ለረጅም ጊዜ የነበረበትን የውሃ አቅርቦት ችግር የፈታ ነው።