ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

የክልሉ መንግስት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።


 

መድረኩ "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፤ ከአደረጃጀት ሽግግር ወደ ልማት ማዕከል" በሚል መሪ ሀሳብ በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ የለውጡ ገፊ ምክንያቶች፣ ከለውጡ በኋላ የተመዘገቡ ስኬቶችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያሳይ የመነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ የልማት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በተለይም ሀገራዊ የእድገት አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም በትውልድ ግንባታ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በመቀጠል የክልሉን ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ክልሉ ያለውን ጸጋ ለይቶ በማልማት ረገድ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

አካታች የፖለቲካ ምህዳርን ከመፍጠር አኳያም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር የመስራት እሳቤን በመጠቀም ለክልሉ ፈጣን እድገት በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በሰጡት አስተያየት፤ በመንግሥት የሚነደፉ አዳዲስ የልማት ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ በመሰራቱ ክልሉ በግብርናውና በሌሎችም መስኮች ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም