ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል

ባህር ዳር፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ):- ህዝበ ሙስሊሙ  የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ።

1447ኛው  የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በአል የፊታችን ረቡዕ በባህር ዳር ከተማ  ጋጃ መስክ በሚገኘው የኢድ መስገጃ ቦታ እንደሚከበር ተገልጿል።

‎የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንትና የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሼህ መሀመድ ኢብራሂም በሰጡት መግለጫ 1447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በዱዓና በስግደት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።

‎‎በዓሉ በአደባባይ የሚከበር በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ሰላሙን በመጠበቅ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማገዝ ሊያከብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎‎‎የሀይማኖቱ ተከታዮች በዕለቱ በነቂስ ወጥተው በኢድ መስገጃ ቦታ ሃይማኖታዊ እሴቱ በሚፈቅደው መሰረት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እንዲያከብሩም አሳስበዋል።

በዓሉ የሰላም፣ የአንድነትና የመከባበር በዓል መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሉ እሴቶቹን በሚያስጠብቅ አግባብ ይከበራል ሲሉም አመልክተዋል።




በዓሉን ስናከብር አንዳችን ለሌላችን ካለን በማካፈል፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዑስታዝ አህመድ ካሳ ናቸው ።

በዓሉ የደስታ፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የመተጋገዝ እንዲሆን መልካም  ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም