7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ለዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለጻ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ለዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለጻ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ አዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶችና ለአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለጻ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሰቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለዲፕሎማቶችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ስለምርጫው ዝግጅት፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ፣ የደህንነት ዝግጅቶች እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝርዝር በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
እንዲሁም የምርጫ ሂደቱ ግልፅ እና ነፃ እንዲሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት ስለመሰራቱ አብራርተዋል።
የቦርዱ ሰብሰቢዋ ምርጫውን በተመለከተ ስለተከናወኑ የቅድመ ምርጫ ስራዎች ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት ለምርጫው ከ50 ሚሊየን በላይ መራጮች መመዝባቸውንና 52 ሺህ 29 የምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።
ለተፈናቃዮች፣ ለወታደሮችና ለተማሪዎች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም የምርጫ ድምጽ መስጫ ካርዶች ለሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች መሰራጨታቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ምርጫው ሰላማዊ፣ አሳታፊ እና ነጻ እንዲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቦርዱ እየሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በበኩላቸው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተከታታይ ሲደረጉ የቆዩ ምርጫዎች ቀጣይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በሀገሪቱ ለተገነባው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የጣለ መሆኑን አብራርተዋል።
ከገለጻው በኋላ በተደረገ ውይይት የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን ስለተደረገው እንቅስቃሴ ግንዛቤ እንዳገኙ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።