ለዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለ1147ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ነዋሪዎቻችን በዓሉን ያለምንም የገበያ ጫና እና እንግልት በደስታ ማክበር እንዲችሉ፣ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እና የበዓል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን እንዲቀርቡ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በተለይም በከተማችን በሚገኙ 7ቱም የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት የሰብል፣ የጥራጥሬ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበው ይገኛሉ ብለዋል።
ሸማቾች በቀላሉ በአቅራቢያቸው መገብየት እንዲችሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ 250 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ክፍት ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል።
በ2 ሺህ 52 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች እና በአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት መጋዘኖች አማካኝነት የዘይት እና የዱቄት ምርቶች በበቂ መጠን ተደራሽ ሆነዋል።
በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች ከተጠቀሱት የገበያ አማራጮች በአቅራቢያችሁ ከሚገኙት መጠቀም ትችላላችሁ ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ጠቁመዋል።