የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው
ደሎ መና፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሮባ ቱርቼ አስታወቁ።
በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ከ936 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ የተገነባው የያዶት የመስኖ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ከመቀነስ ባለፈ፤ ለእንስሳት የመጠጥ ውኃ አገልግሎት የሚውል መሆኑም ተመላክቷል።
አቶ ሮባ ቱርቼ በምረቃው ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
መንግሥት የአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያጋጥመውን ድርቅ እንዲቋቋም በክልል ደረጃ ከ166 የሚበልጡ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል።
ከተጠናቀቁት የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 66 የሚሆኑት ለሰውና ለእንስሳት መጠጥ ጭምር አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው የያዶት የመስኖ ፕሮጀክት ከ3 ሺህ ሔክታር የሚበልጥ መሬት በማልማት ከ6 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፤ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን ኑሮ በማሻሻል በኩል ከፍተኛ ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ከ1 ሺህ 700 የሚበልጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ከ4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተገንብተው እየተመረቁ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
የክልሉ መንግሥት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያረጋገጡት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ መንግሥቱ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው።
የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቆላማና ዝናብ አጠር አካባቢዎች ዘላቂ ልማት ዕቅድ በመንደፍ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቋቋም በትጋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የክልሉ መንግሥት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለውጤት በማብቃት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።