በብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
በብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
ጉኑኖ ሐሙስ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ተናገሩ።
በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ እና የዳሞት ሶሬ ወረዳ በጥምረት ያዘጋጁት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ በጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ተካሂዷል።
ሚኒስትር ሸዊት በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በፓርቲው የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በዞኑ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ እና ኮሪደርን ጨምሮ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በፓርቲው መሪነት በተከናወኑ ሥራዎች የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዩኔስኮ መመዝገቡን አውስተው፤ የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠል የሕዝቡ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የሕዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የፈቱ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።
በፓርቲው መሪነት እንደ ወላይታ ዞን የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እየተፈቱ መጥተዋል ብለዋል።
ይህንን የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ዋጃ በበኩላቸው፤ ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በዚህም ከ500 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም ሌሎች ልማቶችን በከተማዋ ማከናወን መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
መንግሥት የወረዳውን ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዘርፎች ተጠቃሚ ያደረጉ ልማቶች እንዲከናወን አድርጓል ያሉት ደግሞ የዳሞት ሶሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉቀን መሸሻ ናቸው።
በዘንድሮ በጀት ዓመት በ150 ሚሊየን ብር ወጪ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የመንገድ፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የ15 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ግንባታ ሥራን ጨምሮ ሌሎችም ልማቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ገጠርን ከከተማ ጋር ለማስተሳሰር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።