ቀጥታ፡

እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አሳድገዋል

መተማ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፡- እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደጋቻውን የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በሽንፋ ወንዝ ላይ 24 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው ተንጠልጣይ የብረት ድልድይ ተመርቆ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የመምሪያ ኃላፊው ዓባይነህ ወረታው በድልድዩ ምረቃ ላይ እንደገለጹት፤ በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አሳድገዋል።




የዚህ አካል የሆነው ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ድልድይ 120 ሜትር ርዝመትና 1 ነጥብ 6 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ድልድዩ በቋራና መተማ ወረዳዎች የሚገኙ ከ45 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ግንባታውም በክልሉ መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቢሮ በጀትና ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መከናወኑን አስረድተዋል።

በቋራ ወረዳ የደላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታመነ ገላጋይ እንደገለጹት፤ የሽንፋ ወንዝ በክረምት ወቅት በውሃ ሙላት ማኅበራዊ ግንኙነትን ከማቋረጡም በላይ የታመመን ሰው ወደ ሕክምና ለማድረስ ያስቸግር ነበር።

አሁን የተገነባው ድልድይ ለአካባቢው ነዋሪ እረፍት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው፤ በግንባታው ለተሳተፉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመተማ ወረዳ የሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ መልኬ በበኩላቸው፤ ድልድዩ የበርካታ ሰዎች ሕይወትና ንብረት ያጠፋውን የሽንፋ ወንዝ እጅ እንዲሰጥ ያደረገ ነው ብለዋል።

ወንዙ በየዓመቱ ለሰው ኅልፈትና ለቤት እንስሳት በጎርፍ መወሰድ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ገልፀው፤ የድልድዩ መሠራት ይህንን ችግር ከማስወገድ ባለፈ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እንደሚያሳልጥም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም