ቀጥታ፡

መከላከያ ሠራዊት በዓለም የሰላም ማስከበር ተልእኮ ታሪክ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፈ አስተማማኝ ሃይል ነው-ጄነራል አበባው ታደሰ

ድሬዳዋ፣ግንቦት 17/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዓለም የሰላም ማስከበር ተልእኮ ታሪክ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፈ አስተማማኝ ሃይል መሆኑን የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ የ22ኛ እና የ23ኛ ሞተራይዝድ ሻለቆች እንዲሁም የሶማሊያ አውሶም የሴክተር 3 እና 4 የሰላም አስከባሪ የሠራዊት አባላትና አመራሮችን አስመርቋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዓለምና በአህጉር ደረጃ በሰላም ማስከበር ተልእኮ የገዘፈ ስምና ዝና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ እየተመዘገበ የሚገኘውን አኩሪ ታሪክና ገድል የአሁኑም ሠራዊት በታላቅ ብቃትና ጀግንነት በማስቀጠል ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዓለም የሰላም ማስከበር ተልእኮ ታሪክ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፈ አስተማማኝ ሃይል መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም ሀገርን በመወከል የሰላም ማስከበር ተልእኮውን በላቀ ብቃት ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በመሆኑም ለዚህ ታላቅ ተልዕኮ የሚሰማሩት የሠራዊቱ አባላት እና አመራሮች በወሰዱት የቅድመ ዘመቻ ስልጠና በመመራት፣ ያላቸውን ልምድና ጀግንነት በመጠቀም፣ ህዝባዊና ወታደራዊ ዲሲፕሊን በማክበር የተሰጣቸውን አደራ በላቀ ብቃት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄነራል አዳምነህ መንግሥቴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ታሪክ የራሷን የማይረሳ አሻራ ማሳረፏን አንስተው አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።

በእለቱ የተመረቁ የሰላም አስከባሪዎችም ይህንን ታሪካዊ ሃላፊነት በከፍተኛ ስነምግባር፣ሙያዊ ታማኝነት፣በሰብዓዊነትና የሀገር ክብርን በመላበስ መወጣት እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አዲሱ ተርፋሳ፤ ትምህርት ቤቱ የሀገር ሉአላዊነት እና ዳር ድንበርን በላቀ ጀግንነት እያስከበሩ የሚገኙ ጀግኖችን እያሰለጠነ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በአለም ሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ያላትን ታላቅ ክብር እና ዝና የሚያስቀጥሉ ወታደሮችን ማሰልጠኑን አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም