ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የሕብረት ሥራ ማህበራትን የማብቃት ሥራው ይጠናከራል-እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፣ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የሕብረት ሥራ ማህበራትን ደግፎ የማብቃት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሀድያ ዞን ሊቻ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የወተት ማምረቻ፣ ማቀነባበሪያና ግብይት ማዕከልን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የሕብረት ሥራ ማህበራትን ደግፎ የማብቃት ጅምሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል።


 

በክልሉ የሕብረት ሥራ ማህበራት በምርጥ ዘርና በግብአት አቅርቦት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሊቻ የሀድያ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የወተት ማምረቻ፣ ማቀነባበሪያና ግብይት ማዕከል ከአርሶ አደሩ የሰበሰበውን የወተት ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ እንደሚያቀርብም አስረድተዋል።

ዩኒየኑ የራሱን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግስት ጠንካራ የሕብረት ሥራ ማህበራትን ለማጠናከር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በበኩላቸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የሆነው የሌማት ትሩፋት ትግበራ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ እያሳደገው ነው።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከቤተሰብ አልፎ በማህበረሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፁት።

ሊቻ የሀድያ ገበሬዎች ሁለገብ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ሽፈራው እንደገለጹት፥ ዩኒየኑ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ እየሰራ ይገኛል።

ዩኒየኑ 85 ሺህ የሚጠጋ አባላት እንዳሉትና ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገቡን ገልጸው፣ በልማት ስራዎቹም ከአባላቱ በተጨማሪ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የወተት ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከአካባቢው አርሶ አደር ወተት በማሰባሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ያቀርባል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉና የሀድያ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዩኒየኑ አባላት ተገኝተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም