የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦የዘንድሮው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 1447ኛውን የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል አስመልክቶ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን በሰጡት መግለጫ፤ በዓሉ የሰላም፣የአብሮነትና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን ስናከብር የመረዳዳት እና የአብሮነት እሴቶቻችንን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ይህንን እሴት በተግባር ለማዋልም ምዕመናን በዓሉን የተቸገሩ ወገኖቻቸውን በመደገፍና በመርዳት ሊያከብሩት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዓሉ የሕዝብ አንድነት ይበልጥ የሚጠናከርበት እና የመረዳዳት እሴቶች የሚጎለብቱበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ማሰብ፣በመረዳዳትና በመደጋገፍ ማክበር ከበዓሉ መንፈስ የሚጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ለሀገር ልማት እና አንድነት ሁሉም ዜጋ በጋራ መቆም እንዳለበት ጠቅሰው፥በዓሉ እነዚህን ሀገራዊ እሴቶች ለማስቀጠል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።
የዘንድሮው 1447ኛው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የፊታችን ረቡዕ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከበር የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት መግለጹ ይታወቃል።