ቀጥታ፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን በመኸር እርሻ ከ339 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ይለማል

ነጌሌ ቦረና፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው የመኸር እርሻ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ339 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ለማልማት ሥራ መጀመሩን የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ዞኑ በአምስት ዋና ዋና ሰብሎች በሚያከናውነው በዚህ የመኸር አዝመራ ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን የጽሕፈት ቤቱ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ ታሪኩ ብዙአየሁ ገልጸዋል።




በዚህም መሠረት በዘጠኝ ወረዳዎች 339 ሺህ ሔክታር እንደሚለማና በልማት ሥራውም ከ293 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እተሳተፉ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የመጀመሪያ ዙር የእርሻ ሥራ መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።

በመኸር አዝመራው በስፋት ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ቦለቄና ማሾ እንደሚለማ ገልጸው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ስልቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግብርና ሥራውም በትራክተር፣ በመስመርና በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም