ምርጫው በስኬት እንዲከናወን የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው- የወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው በስኬት እንዲከናወን የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው- የወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች
ደሴ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የአካባቢያችንን ሰላም በማስከበር የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በወረባቦ ወረዳ የቢስቲማ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ኃይሌ ዮሴፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መብታቸውን ተጠቅመው የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አንድነታቸውን ጠብቀው የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት ኑሩ መሀመድ በበኩሉ፤ የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ምርጫው ውጤታማ እንዲሆን ከምናደርገው ጥረት በተጓዳኝ የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብሏል።
ዕድሜው 18 ዓመት በመሙላቱ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን በጉጉት እየጠበቀ መሆኑንም ጠቁሟል።
ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ በወረዳው የ04 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሉባባ ይማም ናቸው።
ከአካባቢያቸው ማኅብረሰብ ጋር በመተባበር የቀበሌያቸውን ሰላም በመጠበቅ የምርጫውን ቀን በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
የ02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሰይድ መሀመድ ደግሞ፤ ምርጫውን ውጤታማና ስኬታማ ለማድረግ እኛም የድርሻችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።
የመራጭነት ካርድ ወስደን ለምንፈልገው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት።