ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቦችን የዘመናት ጥያቄ መልሷል - ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቦችን የዘመናት ጥያቄ መልሷል - ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቦችን የዘመናት ጥያቄ በተግባር የመለሰና ተጠቃሚነትን ያጎለበተ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
ፓርቲው በሐረሪ ክልል ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ለረዥም ጊዜ ሲነሱ የነበሩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በሕግና በውይይት አግባብነት ምላሽ እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ፓርቲው ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ማከናወኑንም አክለዋል።
በተለይም በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።
በኮሪደር ልማትና ቱሪዝም ዘርፍ የሐረርን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ አበረታች ሥራዎች ማከናወኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ፓርቲው የገባውን ቃልና የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች ዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠራና ውጤቱም በተጨባጭ እየታየ እንዳለ ተናግረዋል።
በፓርቲው የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው፤ ብልጽግና ፓርቲ አሰባሳቢ የጋራ ትርክትን በመገንባት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት፣ ብዝኃነት ተከብሮ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ማከናወኑን አብራርተዋል።
በለውጡ ዓመታት ፓርቲው ያስመዘገባቸውን ድሎችና ትሩፋቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት ማድረጉንም አመላክተዋል።