ቀጥታ፡

ለሀገር የተሻለ ይሰራል ለምንለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል-የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች

አርባ ምንጭ፤ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላላ ምርጫው ለሀገር ይበጃል፤ለህዝብም የተሻለ ይሰራል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ለምለም ተስፋዬ ሀገርና ህዝብን በልማት ወደፊት ያራምዳል ለምትለው ፓርቲ ድምጿን ለመስጠት የምርጫውን ቀን እየጠበቀች መሆኑን ተናግራለች።

ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ነው የገለጸችው።

ሌላዋ ወጣት መድሃኒት ተመስገን በበኩሏ እንዳለችው፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አንድ ድምጽ ዋጋ እንዳለው ተረድታ ካርዷን እንደማታባክን ተናግራለች።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የክርክር መድረኮችን መከታተሌ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት አስችሎኛል ብላለች።

ወጣት እሱባለው መምህሩ እና አማኑኤል አብዮት በበኩላቸው፥ ምርጫ በቀጣይ ሀገር የሚመራ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻነት የሚመረጥበት መሆኑን አንስታለች።

ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት እንዲችሉ በመገናኛ ብዙሀንና በተለያየ መንገድ ፓርቲዎች ሲያደርጓቸው የነበሩ ቅስቀሳዎችን ሲከታተሉ እንደነበርም ገልጸዋል።

መራጩ ያወጣውን የምርጫ ካርድ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም