ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሩብ ፍጻሜው መቻልን በመለያ ምት በማሸነፍ አራት ውስጥ ገብቷል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በሩብ ፍጻሜው ቦዲቲ ከተማን 3 ለ 2 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ ይገናኛሉ።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ተገናኝተው መቀሌ 70 እንደርታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ፍፁም አለሙ እና ኮትዲቯራዊው አብዱላጢፍ ባምባ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ዳዊት ገብሩ ለወልዋሎ ግቧን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ በ40 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በ34 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የጨዋታው አሸናፊ ቡድን በፍጻሜው ከሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን አሸናፊ ጋር ይጫወታል።