የአፍሪካ ቀን - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቀን
አዲስ አበባ፤ግንቦት 17/2018 ኢዜአ)፦ 63ኛው የአፍሪካ ቀን “የ63 ዓመታትን ዓመታት አንድነት፣ ትስስር እና ልማት፣ አብረን እናክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ይከበራል።
የአፍሪካ አገራትና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አፍሪካዊ ዳያስፖራዎችም ቀኑን በተለያዩ ሁነቶች ያከብሩታል።
በአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ቀኑ ዛሬ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
ህብረቱ ባወጣው መግለጫ የዘንድሮው የአፍሪካ ቀን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) የተመሰረተበት 63ኛ ዓመት ታስቦ እንደሚውል አመልክቷል።
የአፍሪካ ቀን ባለፉት ሁለት ቀናት በስፖርታዊ ውድድሮች፣አውደ ርዕዮች፣ባዛር፣ የመዝናኛ ጨዋታዎች እና በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር ቆይቷል።
የቀኑ አከባባር ማጠቃለያ ስነ ስርዓት ዛሬ በአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአባል ሀገራት ተወካዮች፣የአፍሪካ ዳያስፖራዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ህብረቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ቀኑ በታሪክና በባህል ሀብታም በሆነችው አፍሪካ የአህጉሪቱ ሕዝቦች እርስ በእርስ የባህል፣ የኪነ ጥበብና ሌሎች ልምዳቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክም ነው።
የአፍሪካ ቀን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከህብረቱ ሰራተኞች ማህበር ጋር በመሆን ከአባል ሀገራት፣ ከህብረቱ አደረጃጀቶች እና ከቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች (RECs) ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።
በየዓመቱ የአፍሪካ ቀን መከበር የጀመረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁን የአፍሪካ ህብረት) እ.ኤ.አ በ1963 መመስረቱን ተከትሎ ነው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መጠሪያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን በተደረገ ጉባዔ ወደ አፍሪካ ህብረት መቀየሩ ይታወሳል።
ቀኑ በየዓመቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ግንቦት 25 ይከበራል። በዓሉ የአፍሪካ ቀን ከመባሉ በፊት የአፍሪካ የነጻነት ቀን እየተባለ ይከበር ነበር።