የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ውሎ - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ውሎ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፦ የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።
ሁሉም የ38ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ተደርገዋል::
የሻምፒዮኖቹ አርሰናል የድል ፌሽታ ሲያነሳ፣ የጎረቤቱ ቶተንሃም ከመውረድ መትረፍ፣ የዌስትሃም ከሊጉ መሰናበት፣ የሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ማረጋገጥ እና የብሩኖ ፈርናንዴዝ አዲስ ክብረ ወሰን፤ እለቱን በክስተቶች የታጀበ አድርጎታል።
በሳምንቱ አጋማሽ ከ22 ዓመታት የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው አርሰናል ለረጅም ጊዜ የናፈቀውን ዋንጫ በደማቅ ስነ ስርዓት አንስቷል።
መድፈኞቹ በሰልኸረስት ፓርክ ባደረጉት ጨዋታ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
ጋብርኤል ጄሱስ እና ኖኒ ማዱዌኬ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ጂን ፍሊፕ ማቴታ የፓላስን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
አርሰናል በ85 ነጥብ ዓመቱን በአንደኝነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በፊት የክሪስታል ፓላስ ተጫዋቾች በግራ እና በቀኝ በመቆም ለሻምፒዮኑ አርሰናል የክብር አቀባበል (Guard of honour) አድርገዋል።
ተከታዩ ማንችስተር ሲቲ በአስቶንቪላ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ኦሊ ዋትኪንስ ለቪላ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥሯል።
አንቶዋን ሴሜኒዮ የሲቲን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።
ሲቲ በ78 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
የውሃ ሰማያዊዎቹ አሰልጣኝ ፔፔ ጋርዲዮላ ከጨዋታው በኋላ ክለቡን በይፋ ተሰናብቷል። በርናንዶ ሲልቫም ሲቲን ተሰናብቷል።
የማንችስተር ሲቲው አርሊንግ ሃላንድ በ27 ጎሎች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ተጠናቋል።
በሊጉ የመዝጊያ ቀን ሲጠበቁ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ላለመውረድ የሚደረግ ትግል ነው።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሜዳው ኤቨርተንን አስተናግዶ 1 ለ 0 በማሸነፍ በ41 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።
ጆአኦ ፓሊኒያ የስፐርስን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ሊድስ ዩናይትድን 3 ለ 0 ቢያሸንፍም ከሊጉ ወርዷል።
ቫለንቲን ካስቴላኖስ፣ጃሬድ ቦወን እና ካሉም ዊልሰን ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ዌስትሃም ዩናይትድ በ39 ነጥብ 18ኛ ደረጃን በመያዝ ከሊጉ ተሰናብቷል።
የለንደኑ ክለብ ከ14 ዓመታት የሊጉ ቆይታ በኋላ ወደ ሻምፒዮንሺፑ ወርዷል።
ሊቨርፑል ከብሬንትፎርድ አንድ አቻ በመለያየት በ60 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን አረጋግጧል።
መሐመድ ሳላህ እና አንዲ ሮበርትሰን ከጨዋታው በኋላ ሊቨርፑልን በይፋ ተሰናብተዋል።
ሰንደርላንድ ቼልሲን 2 ለ 1 በመርታት በ54 ነጥብ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊነት ትኬቱን ቆርጧል።
ቦርንማውዝ ሌላኛው የዩሮፓ ተሳታፊ ክለብ ነው።
ቡዱኑ ዛሬ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር አንድ አቻ በመለያየት በ57 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ቼልሲ በ52 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዞ በመጨረስ ከአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ውጪ ሆኗል።
ማንችስተር ዩናይትድ ብራይተንን 3 ለ 0 አሸንፏል።
በአሜክስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፓትሪክ ዶርጉ፣ ብሪያን ምቡዌሞ እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ለዶርጉ ጎል መቆጠር እጁ የነበረበት ብሩኖ ፈርናንዴዝ በዓመቱ 21 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
ከዚህ ቀደም ቲዬሪ ሄነሪ እና ኬቨን ደ ብሮይን (በተመሳሳይ 20 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል) በጣምራ ይዘው የነበሩትን ክብረ ወሰን አሻሽሏል።
ፈርናንዴዝ ትናንት የሊጉ የዓመቱ ምርጣ ተጫዋች በመባል መመረጡ አይዘነጋም።
ዩናይትድ በ71 ነጥብ ሶስተኛ ሆኖ ዓመቱን አጠናቋል።
ብራይተን በ53 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በኮንፍረንስ ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል።
ፋልሃም ኒውካስትል ዩናይትድን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ወራጆቹ በርንሌይ እና ዎልቭስ ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እስከ መጨረሻው ደቂቃ በድራማ እና ትዕይንቶች ታጅቦ ተጠናቋል።