ቀጥታ፡

ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ አዲስ የአርበኝነት ገድልን መጻፍ ይገባል - ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፦ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ አዲስ የአርበኝነት ገድልን መጻፍ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ "ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የአደባባይ የሰላም እና አብሮነት የጸሎት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ አራዳ ፓርክ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች በመርሃ ግብሩ  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ለሰው ልጆች እድል እና ፈተና ይዞ መምጣቱን በአግባቡ መረዳት ይገባል።

ኢትዮጵያ ሁሉንም የምታሰባስብ ጥላ መሆኗን ገልጸው በውስጧ ያሉ ልዩነቶቿም አጥር ሳይሆን በህብረ ቀለም የደመቀ ውበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዘመን ተሻጋሪ ጽኑ ታሪክ ባለቤት መሆኗን አውስተው፤ የኢትዮጵያዊነት ልዕልናው እና የማሸነፊያ ሚስጥር ቁልፉ በአባቶች እና በእናቶች ጸሎት መሆኑ የታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።

ሰላም የኔ ከምንለው አመለካከት እና ፍላጎት በላይ ናት ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ አንድነትን እና ሰላምን ለማጽናት ሳያቋርጡ በጸሎት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተው፤ ጸሎት የልብ ትስስርን ለመፍጠር የሚረዳ የመንፈስ አንድነትን የሚገነባ ድልድይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሁሉም የምትመችና የምትበቃ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ አዲስ የአርበኝነት ገድልን መጻፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በአንድነት ለሀገር ሰላም እና እድገት መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ፤ በሥራ በመጠንከርና በመትጋት ድህነትን መዋጋት አለብን ነው ያሉት።

በበጎ የሚወሳ አሻራ ለማኖር የአባቶቻችንን አደራ እንወጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም