ቀጥታ፡

አርብቶ አደሩ አካባቢ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያሳድጉ ናቸው

ሰመራ፣ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፡- በአርብቶ አደሩ አካባቢ  የተገነቡ የልማት ፐሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያሳድጉ መሆኑን የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ  ኡመር ኑር ገለጹ።

በቂልበቲ ረሱ ዞን መጋሌ ወረዳ የህብረተሰቡን የልማት  ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ  የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ስራ ገብተዋል።


 

ከተመረቁት  ፕሮጀክቶች   ውስጥ በ10 ሚሊየን ብር የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋም ይገኝበታል።

የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር  በወቅቱ እንደገለጹት በአርብቶአደሩ አካባቢ የተገነቡ የልማት ፐሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያሳድጉ ናቸው።

በተለይም የመጠጥ ውሃ ግንባታው እናቶች ውሃ ፍለጋ የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞ በማስቀረት ጉልበትና ጊዜያቸውን በልማት ለማዋል እንደሚያስቻላቸው  ተናግረዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

የአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ አቶ አህመድ ሻሚ በበኩላቸው ለአርብቶ አደሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ  ለማድረግ  ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አሁን ላይ ለምረቃ የበቃው  የውሀ ፕሮጀክትም  በፀሃይ  ሐይል የሚሰራና  የወረዳውን  የንፁህ መጠጥ ውሀ  አቅርቦት የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋሙን  ለመገንባት  10 ሚለየን ብር ወጭ መደረጉን  ተናግረዋል።

የመጋሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሸኸበራ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቀው የውሀ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አንሰተዋል።


 

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋሙ ለረጅም ጊዜ አገልግልት እንዲሰጥ   ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በእለቱ እድሳት የተደረገላቸው ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤትና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም