ቀጥታ፡

ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የዘላቂ ሰላም እና ዕድገት መሰረታችን ነው - ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፦ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የዘላቂ ሰላም እና ዕድገት መሰረታችን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

ሀገር አቀፍ የአደባባይ የሰላም እና አብሮነት የጸሎት መርሀ ግብር በመካሄድ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  "ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን"  በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የአደባባይ የሰላም እና አብሮነት የጸሎት መርሀ ግብር በማካሄድ ላይ ነው።

በአራዳ ፓርክ እየተካሄደ ባለው መርሀ ግብር የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ለሰው ልጆች እድል እና ፈተና ይዞ መምጣቱን በአግባቡ መረዳት ይገባል።

ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የጽኑ ታሪክ ባለቤት መሆኗን አውስተው፤ አባቶች ፈጣሪን በጋራ ጸሎት ለሀገራቸው ሰላምና አንድነት የሚጸልዩላት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኔ ከምንለው አመለካከት እና ፍላጎት በላይ ናት ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ አንድነትን እና ሰላምን ለማጽናት ሳያቋርጡ በጸሎት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር አዲስ የአርበኝነት ገድል መጻፍ እንደሚገባ አመላክተው፤ ጸሎት የልብ ትስስርን ለመፍጠር የሚረዳ የመንፈስ አንድነትን የሚገነባ ድልድይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በአንድነት ለሀገር ሰላም እና እድገት መስራት እንደሚገባ ያመለከቱት ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ፤ በስር በመጠንከርና በመትጋት ድህነትን መዋጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

በበጎ የሚወሳ አሻራ ለማኖር የአባቶቻችንን አደራ እንወጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም