ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማህበረሰቡን የመልማትና የማደግ ጥያቄ በመመለስ ለውጥ ማምጣት ችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማህበረሰቡን የመልማትና የማደግ ጥያቄ በመመለስ ለውጥ ማምጣት ችሏል
ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት16/2018 (ኢዜአ)፡ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማህበረሰቡን የመልማት እና የማደግ ጥያቄዎችን በየደረጃው ምላሽ በመስጠት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ።
ብልጽግና ፓርቲ በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ አንበር ከተማ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዷል።
"በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ፣ ኢትዮጵያን ወደ ተምሣሌት ሀገር" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ የወረዳው አመራሮችን ጨምሮ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን በማከናወን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማህበረሰቡን የመልማት፣ የማደግ እና የለውጥ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ በተሰሩ ስራዎች እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
አሁንም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች ታቅደው እየተተገበሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ይኸንኑ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠልም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲውን በመምረጥ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የስልጡንነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርጫው ሰላማዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማኝነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲከናወንም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የአነደድ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ድረስ በበኩላቸው፤ ምርጫ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የማይቀለበስ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚረጋገጥበት እና ዜጎች የሚሆናቸውን ፓርቲ ለመምረጥ ነጻነት የሚጎናጸፉበት አንደሚሆንም ገልፀዋል።
መንግስት ከዚህ በፊት ለህዝብ ቃል የገባቸውን የልማት አጀንዳዎች በየደረጃው እየመለሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለወደፊትም የለማች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ፓርቲው የቤት ስራ ይወስዳል ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ የተሳተፉት ወይዘሮ አልማው ወንዴ እንዳሉት፤ እንደ ሀገር ልማት፣ እድገት እና ሰላም ስለምንፈልግ ይህን ሊያስቀጥል የሚችለውን ፓርቲ እንመርጣለን ብለዋል።
ከምንም በላይ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
አቶ ዳንኤል ታደሰ በበኩላቸው ምርጫ ሀገርን ለማስቀጠል የሚደረግ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።
እሳቸውም ሰላማዊ ምርጫ ተካሄዶ ሀገር እንድትቀጥል ለህዝብ የልማት ተጠቃሚነትና ሰላም መረጋገጥ የሚሰራውን ፓርቲ በመለየት ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።