የዳውሮ እና የኮንታ ዞን ነዋሪዎች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራዊያዊ ሥርአት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዳውሮ እና የኮንታ ዞን ነዋሪዎች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራዊያዊ ሥርአት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል
ቦንጋ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፡-ይበጀኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የዳውሮ እና የኮንታ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዳውሮ እና የኮንታ ዞን ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ወስደው የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት አየለ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር እድገት የተሻለ አማራጭ ሀሳብ ይዞ የቀረበን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ በመገናኛ ብዙሃን ሲቀርቡ የነበሩ ክርክሮችን በትኩረት መከታተላቸውን አንስተዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ መሰረት በመሆኑ የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት ለዚህም በድምጻቸው መሪያቸውን ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው በዞኑ የቶጫ ወረዳ ነዋሪ አቶ ታምራት ይፍሩ በበኩላቸው፣ ይበጀኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ካርዳቸው ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች በወሰዱት ካርድ ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በነጻነት በመስጠት ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን እንዲወጡም መክረዋል፡፡
በኮንታ ዞን የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ነዋሪ አቶ አድነው አባተ፣ በወሰዱት ካርድ የሀገርን ብልጽግናና ብሔራዊ ጥቅም ያስጠብቃል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መወሰናቸውን ገልፀዋል።
ምርጫ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ በሂደቱም አንድ ድምጽ ዋጋ እንዳለው ዜጎች መረዳትእንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አቶ አረጋ አስፋው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚስችላቸውን ካርድ ይዘው የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ ነው፡፡
ምርጫ በአምስት ዓመት አንዴ የሚመጣ ትልቅ ሀገራዊ ኩነት በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡት ገልጸው፣ በምርጫውም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፅ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለእዚህም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን የተላለፉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በአግባቡ ሲከታተሉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።