በሐረሪ ክልል አቮካዶን በተሻለ ደረጃ በማምረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ወደ ስራ ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል አቮካዶን በተሻለ ደረጃ በማምረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ወደ ስራ ተገብቷል
ሐረር፣ ግንቦት 16/2018(ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል የአቮካዶ ልማትን በተሻለ ደረጃ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ያላቸውንና አምራች አርሶ አደሮችን በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደ አቮካዶ ያሉ ከፍተኛ እሴት ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች በስፋት እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የሐረሪ ክልልም ያለውን የተወሰነ የእርሻ መሬት በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርታማነትን ለመጨመርና የአካባቢውን ማህበረሰብ የውስጥ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያቀደውን ስራ ስኬታማ ለማድረግ፣ የአመራሩና የባለሙያው አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑ ይገለጻል።
በክልሉ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ለማስጀመር በልማቱ ዙሪያ ለዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በማያያዝ አቮካዶን የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው።
ይህንን ተግባር ለማጎልበት በክልሉ በብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም የተለያዩ ስራዎች ተቀርጸው ተግባራዊ የማድረግ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህም የአቮካዶ ልማት የሚከናወንበት ቦታን የመለየት ስራ መከናወኑን የተናገሩት አቶ ነስረዲን በክልሉ በአራቱ የገጠርና ከተማ ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በተለይም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአቮካዶ ልማት የዝግጅት ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው ችግኝ የማፍላትና የማዳቀል እንዲሁም የአርሶ አደሮችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ይህ የአቮካዶ ልማት ኢንሼቲቭ በቴክኖሎጂ በማዘመን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ምርቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል አየር ፀባይ ለአቮካዶ ልማት ምቹ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሬድዋን ናቸው።
ይህ ፕሮግራም በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ከማድረጉ ባለፈ ለወጣቶችም የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።