7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትኃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ እየሰራን ነው-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትኃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ እየሰራን ነው-የፖለቲካ ፓርቲዎች
ጋምቤላ ግንቦት 16/2018(ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትኃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለፁ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የምዝገባ፣ የዕጩዎች ጥቆማ እና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ይገኛል።
በተለይም ምርጫው ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፣ ፓርቲዎቹም የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብን በማክበርና ደጋፊዎቻቸውን በማንቃት ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።
በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢዜአ እንደገለፁት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ፍትኃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ እየሰሩ ነው።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ተወካይ አቶ ኡፓዲ አኳይ እንዳሉት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም እንከን እንዲከናወን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ ናቸው።
በተለይም ዜጎች ያመኑበትን ፓርቲ በነፃነት መምረጥ እንዲችሉ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ሰፊ ስራዎች ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
ፓርቲው ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ፕሮግራሞቹንና ፖሊሲዎቹን ለመራጩ ህዝብ ያለምንም ችግር ማቅረቡን ጠቅሰዋል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ካለፉት የምርጫ ጊዜያት በተሻለ መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ተወካይ አቶ ሬክ ኖክ ናቸው።
የፓርቲዎችን ማኒፌስቶ መራጩ ህዝብ በቀላሉ በሚሰማውና በሚረዳው ቋንቋ እንዲቀርብ መደረጉን ለአብነት በማንሳት።
የህዳሴ ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ተወካይ መምህር ሻምበል ቶላ በበኩላቸው በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግስት ለመመስረት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ህዳሴ ፓርቲ በነፃነት ፕሮግራሞቹንና ፖሊሲዎቹን በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮች ማስተዋወቁን ገልፀው ሂደቱም ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር አንስተዋል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ህዳሴ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
መራጩ ህዝብም በወሰደው ካርድ ሀገርንና ህዝብን የሚጠቅም ሀሳብ ያለውን ፓርቲ በመምረጥ ህገ-መንግስታዊ መብቱን ሊጠቀም እንደሚገባ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ አሳስበዋል።