ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠንካራ የተቋም ግንባታና ብቁ የፖሊስ ሃይል የማፍራት ስራ በውጤታማነት እንደቀጠለ ነው - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

ድሬደዋ ፣ ግንቦት 16/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠንካራ የተቋም ግንባታና ብቁ የፖሊስ ሃይል የማፍራት ስራ በውጤታማነት እንደቀጠለ  የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በድሬደዋ ያስገነባውን የምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ዘመናዊ ማዕከል አስመርቆ አገልግሎት አስጀምሯል።


 

ማዕከሉን መርቀው በይፋ ስራ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤  ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዘመናዊና ጠንካራ አደረጃጀት በመታገዝ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመወጣት የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በድሬዳዋ የተገነባው ዘመናዊ የፈጥኖ ደራሽ  ማዕከልም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን አንስተው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠንካራ የተቋም ግንባታና ብቁ የፖሊስ ሃይል የማፍራት ስራ በውጤታማነት እንደቀጠለ ገልጸዋል።


 

የማዕከሉ ስራ መጀመር በኢትዮጵያ ዋነኛ የገቢና ወጪ እንቅስቃሴ እንዲሁም ቀጣናውን በአስተማማኝ መልኩ ለማስጠበቅ የተደመረ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከሉ የወንጀል ምርመራ ኃይልን በማደራጀት ወንጀልን በላቀ እና በተሻለ ደረጃ ለመከላከልም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዘመናዊ የተቋማት ግንባታና የሰው ሃይል ልማትን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ በድሬዳዋ የተገነባው ዘመናዊ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማዕከሉ ለምስራቅ ተጎራባች ክልሎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተዋል።

የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎችን በአስተማማኝ መንገድ ለማካሄድና ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በማዕከሉ ለሚከናወኑ ስራዎች አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለማዕከሉ መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ድርጅቶች ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም