የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፡-የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
የመደመር ማሳያ
ከሳምንቱ አበይት ክስተቶች መካከል የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች በአሶሳ ከተማ ያስገነቡት የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የህንፃ ምረቃ ይጠቀሳል። በክልሎቹ ትብብር የተከናወነው የህንፃ ግንባታ በመደመር እሳቤ የዜጎችን የጋራ ሰላም ለማስጠበቅና የልማት ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ ጥረት ማሳያ ነው።
መርሃ ግብሩ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) የተገኙበት ነበር።
በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ላይ ያተኮረው መድረክ
በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ የተካሄደውና በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ያተኮረው ፎረምም በእዚህ ሳምንት ዐበይት ጉዳይ ነበር። ፎረሙ የተካሄደው “ቀጣናዊ ተቋማትን ማጠናከር ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሆን የተዘጋጀውም በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በሰላም እና ፖለቲካዊ ምክክር ማዕከል (CRPP)፣ በሶማሌ ክልል መንግስት እና በሌሎች አጋር አካላት ነው።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ መድረኩ የውጭ ተዋናዮች ሳይገቡበት የቀጣናው አካላት በራሳቸው ጉዳይ፣ ፖሊሲና እርስ በእርስ ግንኙነት ላይ ብቻ የሚመክሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ግልጽነትን ለመፍጠርና ጠንካራ ትስስርን ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑም በቀጣናው ግጭቶች ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚረዳ ነው ያነሱት። ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ምሁራን ጥልቅ ውይይት በማድረግ ለቀጣናው ፈተናዎች ተጨባጭ መፍትሄና አቅጣጫ እንዲያስቀምጡም ያግዛል ብለዋል።
የጉባ ላይ ብስራቶች ተግባራዊ ልማት
የሳምንቱ የበረራ ቅኝታችን የሚጀምረው ወደ ሶማሌ ክልል ጎዴ ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በስፍራው እየተገነባ ያለውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላም በምግብ ራስን የመቻል ጥረትን ለማሳካት የመሬት፣ ውሃ እና የሚያለማ የሰው ሃይል አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ በቂ ሃብት ያላት መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህን ካሟላን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሚተርፍ ነገር ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ የኒውክለር ሃይል ማመንጫ፣ የቢሾፍቱ አየር መንገድ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የቤቶች ልማት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጓቸው የጉባ ብስራቶች መሆናቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ መርቀው ስራ ያስጀምሩትም በዚሁ ሳምንት ነበር።
በግራንዴር ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው ፋብሪካ፣ መሰረት ልማቱ በ300 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የሴራሚክና የፎርሲሌን ንጣፎች ማምረቻ ፋብሪካ ነው። የፋብሪካው መገንባት የውጭ ምርት ጥገኝነት ከመቀነስ ባለፈ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት መሆኑ ታውቋል።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ ጉብኝት
በዚሁ ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ወደ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመጓዝ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል። በድሬዳዋ ቆይታቸው ብርቱካንና ሌሎች የፍራፍሬ ልማት ሥራዎች እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ልማት ስራን ተመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የግብርና ልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል። ከጉብኝታቸው በኋላ ባስተላለፉት መልእክትም የጋራ ሙለታ ተፈጥሯዊ የልማት ፀጋና ከፍታም ታሪክን፣ ውብ መልክዓ ተፈጥሮን የታደለ፣ የኢትዮጵያን ሜዳና ተራሮች ምርት የሚታፈስባቸው የማድረግ ሀገራዊ ጉዞ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን የማድረግ ጥረት ማሳያዎች
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በኮንታ ዞን ኮይሻ ወረዳ ተገኝተው 142 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የንፁህ መጠጥ ውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርቀው ሥራ ያስጀመሩትም በዚህ ሳምንት ነበር። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር በለውጡ ዓመታት ከልማት የራቁ አካባቢዎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ መሰራቱን አንስተዋል። የኮንታ ኮይሻ ወረዳ የንጽህ መጠጥ ውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶች ለዚሁ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የተገነቡ የንጹህ መጠጥ እና የመስኖ ፕሮጀክቶች መርቀው ለአገልግሎት አብቅተዋል።
የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በተለይ አርብቶ አደሮች ውሃ ለማግኘት ሩቅ አካባቢዎች ሲሄዱ ይደርስባቸው የነበረን እንግልት የሚያስቀር ነው። የመስኖ ፕሮጀክቱም የክልሉ አርብቶና አርሶ አደሮች በአካባቢው ያለውን ሰፊ መሬት በማልማት ምርታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የፌዴራልና የክልሉ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሲዳማ ክልልም በፌደራል መንግስት ድጋፍ በ460 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዳዬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታም ተመርቋል። ፕሮጀክቱ 75 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ፕሮጀክቱ የተመረቀው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) ነው።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ከ543 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 52 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መመረቃቸው ሌላው የሳምንቱ ክስተት ነበር። በዞኑ ለምረቃ ከበቁ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዞኑ ቃሉ ወረዳ በ365 ሚሊዮን ብር የተገነባውን የዲርማ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክትንም መርቀዋል።
ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ የሚደረግበት የሃዋሳ ከተማ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ የማስጀመሪያ መርሃ ግብርም በዚህ ሳምንት ተካሂዳል። ለፕሮጀክቱ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ያስጀመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የፕሮጀክቱ ግንበታ ሲጠናቀቀ ሀዋሳ ከተማዋን ጽዱ በማድረግ የቱሪዝምና የኢንቨስመንት ማዕከልነቷን ያሳድገዋል ተብሏል። አቶ ደስታ የፕሮጀክቱ ግንባታ መንግስት ለከተሞች እድገት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል ሲሉም ነው የጠቀሱት።
የከሰም መስኖ ግድብ
የከሰም መስኖ ግድብ የጥገና ማሻሻያ ፕሮጀክትም በዚሁ ሳምንት ተመርቆ ሥራ ጀመሯል። ፕሮጀክቱ የተመረቀው በአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ነው። የማሻሻያ ግንባታ መጠናቀቅ ከሚሰጠው ዘላቂ የልማት አገልግሎት ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ ለዓመታት ሲፈታተን የነበረውን የጎርፍ ስጋት ያስቀራል ተብሏል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትር አብርሃም (ዶ/ር) እንዳሉት፥ የከሰም መስኖ ግድብ ቀደም ሲል በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እንደ ትልቅ ስጋት ይታይ ነበር። የጥገና ማሻሻያው በአካባቢው ማህበረሰብ የነበረውን ይህን የአደጋ ስጋት በማስቀረት ግድቡን ለታለመለት የመስኖ ልማት ለማዋል የሚያስችል ነው። ለፕሮጀክቱም 2 ቢሊዮን ብር በጀት መውጣቱን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ ፕሮጀክቱ ህብረተሰቡን ከስጋት ያዳነ እና በርካታ ጥቅሞች ያሉት ነው ብለዋል። የግድቡ ጥገና መጠናቀቅ የሀዝቡን የቆየ ጥያቄ የፈታ መሆኑንም አንስተዋል።
የግንቦት - ታላቁ ሁነት
ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ድምጻቸውን ለመስጠት የተመዘገቡበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል። የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና የምርጫ ሂደቱን ስኬታማ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ አጠቃላይ ዜጎችና የሚመለከታቸው ሁሉ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በዚሁ ሳምንት "ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚ
ና" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር በአዳማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎና የዳበረ የዴሞክራሲ ልምምድ የታየበት መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅም መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ከተረጅነት የመውጣት ሀገራዊ ጥረት
በድሬዳዋ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የውይይት መድረክም ሌላው የእዚህ ሳምንት ዓቢይ ጉዳይ ነው። መድረኩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የግብርና ሚኒስቴር በመተባበር ያዘጋጁት ነው። በመድረኩም በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑ ተነስቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቂና የተሟላ የውሃ ሀብት፣ የተማረና አምራች የሆነ ወጣት የሰው ኃይል እንዲሁም ለም የመሬት ፀጋዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗ በማልማት እድገትና ማንሳራራትን ማስቀጠል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
ለእዚህም ዋናው መሠረታዊ ጉዳይም ያሉ አቅሞችን በመለየትና ህዝብን ወደ ላቀ ምርታማነት ደረጃ በማሸጋገር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡን ሥራ በላቀ ደረጃ ማስቀጠል መቻል መሆኑን አንስተዋል።
ለሰላም ጥሪ የተሰጠ ምላሽ
የሠላም ጥሪን የተቀበሉ የአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የመረከብ፣ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግና የመልሶ ማቋቋም (ዲዲአር) መርሀግብርም በዚህ ሳምንት ተከናውኗል። በብሔራዊ ተሀድሶ ማዕከል ጠዳ ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በተዘጋጀው መርሀግብር ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ የቀድሞ ታጣቂዎች ከስልጠና በኋላ ከምንም በላይ የሰላም ዘብ ሆነው የበደሉትን ህዝብ ለመካስ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ሠላምን አማራጭ በማድረግና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለሠላም ያደረጉት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፣ መንግስት ለሠላም ባለው ጽኑ አቋምና ፍላጎት የሠላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና እንዲያልፉ በማድረግ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ እያደረገ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በኮምቦልቻ የስልጠና ማዕከል ስልጠና የጀመሩ መሆኑ ይታወቃል።
ሐረር- ፕሮጀክቶች ምረቃ
የሐረሪ ክለል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙትን የሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጉብኝትም ሌላው የእዚህ ሳምንት ኩነት ነበር። በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በተሻለ አፈጻጸም ላይ ይገኛሉ።
በተለይም የሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባት የክልሉን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የበለጠ በማሳደግ ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ነው ያነሱት።
በዘመናዊ ትምህርት የታነፀና በእውቀት የበለፀገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በማፍራት ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሮጀክቶቹ በፍጥነትና በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማስቻል በአስተዳደሩ በኩል ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
የጂግጂጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት
672 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የጂግጂጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በይፋ የተመረቀውም በዚህ ሳምንት ነው።
በምረቃው ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን፣ የክልሉ የመንገዶች ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢድሪስ ሙሴ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንደገለጹት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የጂግጂጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት የከተማውን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚያስችል ነው። የከተማውን ገፅታ በመለወጥ ረገድም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ያነሱት።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክቱ የጂግጂጋ ከተማን ልማትና ዕድገት በማፋጠን በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የመንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን አስተዳደሩ ሀገራዊ የመንገድ መሰረተ ልማት ዕቅድን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የጂግጂጋ ከተማ ተለዋጭ የመንገድ ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 7 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 30 ሜትር ስፋት እንዳለውም ታውቋል።