የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ያከናውናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ያከናውናል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከብሩንዲ ጋር ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 8 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወቃል።
ተጋጣሚዋ ብሩንዲ በመጀመሪያው ዙር ማላዊን በአጠቃላይ ውጤት 4 ለ 2 አሸፋለች።
አሰልጣኝ ራውዳ አሊ ለማጣሪያ ጨዋታው ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ ብሔራዊ ቡድኑ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ራውዳ የመጀመሪያ ጥሪ ከተደረገላቸው 30 ተጫዋቾችች መካከል አምስቱን በመቀነስ ቡድኑ ዝግጅቱን ቀጥሏል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአበበ በቂላ ስታዲየም ማድረጉንና ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በፓትሪክ ሳንጋዋ የሚመራው የብሩንዲ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታው ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ቡጁምቡራ ላይ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ትጫወታለች።
10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች።
በማጣሪያ የሚያልፉ አራት የአፍሪካ ሀገራት በሶስት ዙሮች በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።