አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለን ስንነሳ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባትን ቅድሚያ በመስጠት ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለን ስንነሳ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባትን ቅድሚያ በመስጠት ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16 /2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለን ስንነሳ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባትን ቅድሚያ በመስጠት ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦሌ ክፍለ ከተማ 5 ስፖርት ማዘውተሪያዎችን፣ 95 የህጻናት መጫዎቻዎችን፣ 6 የህጻናት ማቆያዎችን (day cars )፣ ካፍቴሪያዎችን፣ አንፊ ትያትሮችን እንዲሁም በርካታ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በተለይ ካፒቴን አበራ ለሚ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገነቡት በ4,900 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ስታዲየም የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ፣ የመሮጫ ትራክ፣ ጥላ ያለው የተመልካች መቀመጫ፣ ለወጣቶች የስራ እድል የሚውሉ ሱቆች፣ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤቶች፣ ጂምናዚየም እና የእቃ ማከማቻ መጋዘንን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
የለሚ ኮሚኒቲ ስታዲየምን ገንብተው ያስረከቡትን ካፒቴን አበራ ለሚን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመሰግናለሁ ያሉት ከንቲባዋ የአካባቢው ነዋሪዎችም ስታዲየሙን በእንክብካቤ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የክፍለ ከተማዉ አመራሮችንም ለሰራችሁት ድንቅ ስራ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።