ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎችን አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎችን አከናውኗል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 16 /2018 (ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን ገለፁ።
የብልፅግና ፓርቲ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃግብር በሸገር ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፓርቲው ደጋፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
ከማለዳው ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪዎችና የፓርቲው ደጋፊዎች በለገጣፎ ስታዲየም በመገኘት ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት ገልፀዋል።
በመርሃግብሩ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እና ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን ብልፅግና ፓርቲ የጀመረውን ሀገር የመገንባትና የልማት ጉዞ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም ጥራትንና ፍጥነትን መመሪያ በማድረግ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በርካታ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ፓርቲው የገባውን ቃልና የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች ዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ውጤቱ በተጨባጭ እየታየ እንዳለ ተናግረዋል።
በክልሉ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በሸገር ከተማ ዘመናዊ ከተማ የመገንባት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የመንገድ መሰረተ ልማቶ፣ የሆስፒታሎችና የትምህርት ቤቶች ግንባታን በማካሄድ ከፍተኛ የማኅበራዊ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
እንዲሁም እንደሀገር የተቀረፁ የግብርና እና የኢኮኖሚ ዕቅዶችን በከተማ ደረጃ ስኬታማ ሥራ ለመስራት ማስቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ተግባርም ብልፅግና የሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታዩ ሰፋፊ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ