ቀጥታ፡

አርሰናል የዋንጫ አቀባበል፣ የአውሮፓ ተሳትፎ ፉክክር፣ የጋርዲዮላ ስንብት እና የቶተንሃምና ዌስትሃም በሊጉ የመቆየት ህልም፦ በሊጉ መዝጊያ ቀን የሚጠበቁ ክስተቶች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16 /2018 (ኢዜአ)፦ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም የጀመረው የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ38ኛ ሳምንት ማጠቃለያ ጨዋታዎች ዛሬ በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።


ከ22 ዓመታት ጥበቃ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው አርሰናል (1ኛ፣ 82 ነጥብ) ወደ ሰልኸረስት ፓርክ በማቅናት ከክሪስታል ፓላስ (15ኛ t፣ 45 ነጥብ) ጋር ይጫወታል።


ደጋፊዎቹ መድፈኞቹ ከጨዋታው በኋላ የሚያደርጉትን ይፋዊ የዋንጫ ርክክብ በጉጉት ይጠብቁታል።
 
 
ከጨዋታው መጀመር በፊት የክሪስታል ፓላስ ተጫዋቾች በግራ እና በቀኝ በመቆም አርሰናል ወደ ሜዳ ሲገባ የክብር አቀባበል (Guard of honour) ያደርጋሉ።

የዛሬው ተቀናቃኛቸው ክሪስታል ፓላስ ይህንን ጨዋታ የሚያደርገው ከስፔኑ ራዮ ቫዮካኖ ጋር ለሚያደርገው የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዋዜማ ላይ ሆኖ ነው።

በሌላ በኩል በሳምንቱ አጋማሽ ከቦርንማውዝ ጋር አንድ አቻ ተለያይቶ የዋንጫ ጉዞው ያበቃው ማንችስተር ሲቲ (2ኛ፣ 78 ነጥብ) ዓመቱን በድል ለመዝጋት ከአስቶንቪላ (4ኛ፣ 62 ነጥብ) ጋር በኢትሃድ ስታዲየም ይጫወታል።
 
በሳምንቱ አጋማሽ ከክለቡ መለያየቱ ይፋ የሆነው ፔፕ ጋርዲዮላ የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

አስቶንቪላ በበኩሉ  ከዩሮፓ ሊግ ዋንጫ የድል ፌሽታ ማግስት ዓመቱን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ይፋለማል።

በመዝጊያው ቀን ትልቁን ትኩረት የሳበው ሌላው ክስተት በለንደኖቹ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ዌስትሃም ዩናይትድ መካከል የሚደረገው የህልውና ፉክክር ነው።

ቶተንሃም ከኤቨርተን፣ ዌስትሃም ደግሞ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአሁኑ ሰዓት ስፐርስ በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ሲገኝ፣ ዌስትሃም በ36 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይገኛል።

የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም በዛሬው ጨዋታ በትንሹ አንድ ነጥብ (አቻ) ካገኘ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል፤ በአንጻሩ ቶተንሃም ተሸንፎ ዌስትሃም ማሸነፍ ከቻለ ግን የዲዘርቢው ስፐርስ ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱ ሲረጋገጥ ዌስትሃም በፕሪሚየር ሊጉ ይቆያል።
 
ከወራጅ ቀጠናው ውጪ ወደ አውሮፓ መድረክ (ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ዩሮፓ ሊግ እና ኮንፍረንስ ሊግ) ለማለፍ የሚደረገው ፍልሚያ እጅግ ተቀራራቢ ሆኗል።

አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል (59 ነጥብ) ከብሬንትፎርድ (9ኛ፣ 52 ነጥብ) ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋግጣል።

ባለፉት 17 ጨዋታዎች ያልተሸነፈውና የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎውን ቀድሞ ያረጋገጠው ቦርንማውዝ (6ኛ፣ 56 ነጥብ) ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር የሚጫወት ሲሆን፤ በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ አስቶንቪላ 5ኛ ሆኖ ማጠናቀቅ (ቪላ የዩሮፓ ሊግ አሸናፊ በመሆኑ ሊጉን 5ኛ ካጠናቀቀ 6ኛ ደረጃ ላይ ያለውን ክለብ 6ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ኮታ ያደርገዋል።

የቦርንማውዝ ሌላኛው ተስፋ የሊቨርፑል መሸነፍ እናኖቲንግሃም ፎረስትን በ6 እና ከዚያ በላይ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ነው።

በተመሳሳይ ሰባት፣ ስምንት እና አስረኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብራይተን (53 ነጥብ)፣ ቼልሲ (52 ነጥብ) እና ሰንደርላንድ (51 ነጥብ) እርስ በእርስ የሚሻሙ ሲሆን ብራይተን ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነጥብ የሚጥል ከሆነ ሰንደርላንድን የሚገጥመው ቼልሲ ወይም ብሬንትፎርድ ሰባተኛ ደረጃን በመንጠቅ የአውሮፓ መድረክ ዕድል ያገኛሉ።

በሌሎች ጨዋታዎች ቀድመው ከሊጉ መውረደቸውን ያረጋገጡት በርንሌይ እና ዎልቭስ እርስ በእርስ ሲገናኙ፣ ፉልሃም ደግሞ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ይጫወታሉ።

በአጠቃላይ የሊጉ መዝጊያ ቀን የአርሰናልን የደመቀ የዋንጫ አነሳስ፣ የለንደኖቹን የሞት ሽረት ያለመውረድ ፉክክር እና እስከ መጨረሻዋ ሰከንድ የሚዘልቀውን የአውሮፓ መድረክ ትንቅንቅ በአንድ ላይ አጣምሮ በክብር፣ በደስታ፣ በለቅሶ እና በጸጸት የታጀበ ታሪካዊ ፍጻሜ ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም