የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አልቻለም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አልቻለም
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ ከ17 ዓመት በታች ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገ የመለያ ጨዋታ ሞዛምቢክ ኢትዮጵያን በመለያ ምት አሸንፋለች።
በመሐመድ ስድስተኛ ስፖርት ኮምፕሌክስ በተካሄደው ጨዋታ አሚር ሚስባህ በ16ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ኢትዮጵያን መሪ አድርጓል።
ዲዬጎ ፔሌምቤ በ57ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፋት ጎል ሞዛምቢክ አቻ ሆናለች።
ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቷል።
በመለያ ምቱም ሞዛምቢክ 5 ለ 4 በማሸነፍ በኳታር አስተናጋጅነት ለሚከናወነው 21ኛው ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።
እንየው ስለሺ ከኢትዮጵያ በኩል ፍጹም ቅጣት ምቱን የሳተ ተጫዋች ነው።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አልቻለም።
በሌላኛው የመለያ መርሐ ግብር ጋና ከዩጋንዳ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዘጋጇ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ኮትዲቯር፣ ካሜሮን፣ ታንዛንያ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል እና አልጄሪያ በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ናቸው።
16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በአፍሪካ ዋንጫው እየተሳተፉ ካሉ 16 ሀገራት መካከል 10ሩ በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናሉ።
በዓለም ዋንጫው ላይ 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።