ባሳለፍነው ሳምንት … - ኢዜአ አማርኛ
ባሳለፍነው ሳምንት …
ከግንቦት 9 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …
👉የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ለአገልግሎት ክፍት መሆን
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ጉዟችን አካል እና የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እመርታ ትልቅ ማሳያ የሆነው የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ፋብሪካው የዓለም ዓቀፍ ጥራትና ተወዳዳሪነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ የሴራሚክ ምርቶችን የሚያቀርብ መሆኑንም ገልጸዋል። ለምርቱ የሚያስፈልጉትን ጥሬ ዕቃዎች ከ80 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥ ዐቅም ያገኛልም ብለዋል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብትና እምቅ ጸጋ የመጠቀም ብቃቷን ከመገንባቱ ባሻገር፤ በውጭ ገቢ ምርቶች ላይ ያለንን ጥገኝነት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል ነው ያሉት።
👉ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ያደረጉት ጉብኝት
ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎዴ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ሥራ የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም የፕሮጀክት ስፍራውን ጎብኝተዋል። በዚሁ ወቅትም፤ ይህ ሥራ ከመሠረተ-ልማት ግንባታም በላይ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት እና በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ኢንቨስትመንት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በፕሮጀክቱ ስፍራ የሚታየው የሥራ ሂደት ፍጥነት አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ግዙፍ እና እጅግ ጠቃሚ ሀገራዊ ፕሮጀክት ለመፈፀም ያለውን ቁርጠኝነት እና ትብብር በሚያንፀባርቅ ሁኔታ በተለያዩ የፕሮጀክቱ ክፍሎች ያሉት ግንባታዎች በዕቅዳችን መሠረት እየተጓዙ ይገኛሉ ሲሉም አረጋግጠዋል።
👉የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት
“የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በተሰኘውና ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉላዊነት ጉዞ ያስመዘገበችው ትልቅ ድል በተበሰረበት ሀገራዊ ጉባዔና ኤግዚቢሽን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተው ነበር። በዚሁ ወቅትም፤ የተመለከቱት የዘርፉ እመርታ እጅግ አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል።
መረጃ የዚህ ዘመን ስትራቴጂካዊ ሀብት እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባበት ቁልፍ የሉዓላዊነት ምሰሶ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የተዋሰ አሊያም በውጭ አካላት ላይ ጥገኛ የሆነ መረጃ ሀገራዊ መሻታችንን ማሳካት ስለማያስችል፤ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ ዐቅም መሰብሰብ እና መተንተን ወሳኝ ግብዓት ነው ብለዋል።
ከሁሉም በላይ፤ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥራ በሀገር ልጆች ዕውቀትና ክኅሎት ሲከወን ማየት ታላቅ ሀገራዊ ኩራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ ትኩረታችን በቁጥር በሚገለጹ ውጤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር በሆኑና በዜጎች ሕይወት በሚታዩ ተጨባጭ ለውጦችም ላይ መሆን አለበት ነው ያሉት።
👉ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሐረሪ ክልል ያደረጉት የልማት ሥራዎች ጉብኝት
ባሳለፍነው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሐረሪ ክልል የልማት ሥራዎች የጎበኙ ሲሆን በወቅቱም፤ በሐረሪ ክልል የተመለከትነው የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ በመቀየሩ ረገድ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
በሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ የተገነቡት ቤቶች የሰዎችን ማደሪያ ከሕጻናትና ከከብቶች ቤት የለዩ፣ የዶሮ እርባታ፣ ሻወርና መፀዳጃ ቤት እንዲሁም የጓሮ የሌማት ትሩፋትን ያካተቱ ሙሉ ፓኬጅ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ጉልበትና ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም፣ በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በሐረር ከተማ እየተከናወኑ ያሉትን የማር፣ የወተትና የዶሮ እርባታ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ በከተማው በኢኒሼቲቩ በግለሰብና በመንግሥት ደረጃ ሼዶችን በመገንባት የማር፣ የወተት፣ የእንቁላልና የአሳ መንደሮችን የማቋቋም ሥራ በስፋት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የአመጋገብ ሥርዓታችንን ከመሠረቱ ለመቀየር እና በምግብ እራስን ለመቻል ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። የእንስሳት፣ የዶሮና ዓሳ ዝርያ ማሻሻልና መኖ ማቀነባበሪያዎች ላይም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ይገኛል ነው ያሉት።
👉የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመት
ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል የእራት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጽናት፣ የዕድገት እና የጥቁር ሕዝብ የከፍታ ዓርማ ነው ብለዋል።
ሀገር ማጽናት የሚቻለው ተቋማትን በማጽናት ነው፤ በዘመናዊ ታሪካችን የገጠሙን የስብራት ወጀቦችን አልፎ፣ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ታሪክ እየጻፈ የተጓዘው አየር መንገዳችን የጽናታችን ግንባር ቀደም ማረጋገጫ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ለሀገራችንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ በመደገፍ፣ ሀገራችንን በአቪዬሽን መሠረተ ልማት ከፍ በማድረግ፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማገዝና በሌሎች ዘርፎች ባለው ግዙፍ አበርክቶው የዕድገታችን ምሰሶ ሆኗልም ነው ያሉት።
ይህ ተቋም በሁለት እግሩ እንዲቆም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ መሪዎችና ሠራተኞች ነበሩት፤ አሁንም አሉት፣ ወደፊትም ይኖሩታል። ይህ የተቋሙ አንጡራ ሀብት በመሆኑ የመንግስት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።