ቀጥታ፡

የአፈር ለምነትን በዘላቂነት የሚጠብቁ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች እየተጠናከሩ ነው

አምቦ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ የአፈር ለምነትን በዘላቂነት የሚጠብቁ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን በመተግበር ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ በአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ በአፈርና ውሃ ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚያግዝ ላብራቶሪ ስራ አስጀምሯል።


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሤ ደቻሳ (ፕ/ር)  እንደገለጹት፤ የአፈር ለምነትን መጠበቅ ለምርትና ምርታማነት እድገት መሰረታዊ በመሆኑ፣ የአፈር ለምነትን የሚቀንሱ ችግሮችን በሳይንሳዊ ዘዴ መለየትና የላብራቶሪ ማዕከላትን ማጠናከር አስፈልጓል።

በአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ስራ የጀመረው የአፈር እና ውሃ ላብራቶሪም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የላብራቶሪው ዋና ዓላማም የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግና የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ እንደሆነ አንስተዋል።

የአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ጀማል ቶላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት ከአካባቢው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ለእጽዋት ጥበቃ የሚውሉ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል።


 

የምርት መጠንን ለመጨመር የሰብል ልማትን የሚደግፉ ሰፋፊ የግብርና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ይህም የአካባቢውን አርሶ አደሮች ከመደገፍ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረጉን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ግብርናን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችንና የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።


 

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ወይዘሮ እሸቱዋ ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ ከግብርና ማዕከሉ ባገኙት ስልጠና በመታገዝ የተሻሻለ የበቆሎ ዝርያ ወስደው በመዝራታቸው፣ ምርታቸው ከበፊቱ እጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም