ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የተቀናጀ የከተማ ግብርና ማዕከል መረቁ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የተቀናጀ የከተማ ግብርና ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው፤ የተቀናጀ የከተማ የግብርና ማዕከሉ በ3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እና 18 ሱቆችን እንዲሁም 18 ሼዶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ለሁሉም የምትመች የጋራ ቤትና ልማቷም አካታች መሆኑን አመልክተዋል።




ባለፈው ሥርዓት አርሶ አደሩ የሚገፋበት፣ መሬቱ ብቻ ተፈልጎ እርሱ የሚዘነጋበት የነበረ በመሆኑ ለለውጡ መምጣት ገፊ ምክንያት እንደነበር አስታውሰዋል።

የአሁኑ የከተማ አስተዳደር አርሶ አደሩን በሁሉም የከተማ ልማት ውስጥ አካቶ አብሮ እንዲለማ እና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ እያደረገ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ለልማት በሚነሳበት ወቅት ተገቢውን ካሳ ከማግኘት ባለፈ ከልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ልህቀት ማዕከል እና ዛሬ በለሚ ኩራ የተመረቀው ማዕከል የዚሁ ማሳያ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።




እነዚህን መሰል ማዕከላት የከተማው ነዋሪ የሚያጋጥመውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እና በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ ያስችላሉ ያሉት ከንቲባዋ፣ አሰራሩ በጋራ ማደግንና ተባብሮ መበልጸግን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን ግዙፍ ስራ በማቀድ፣ በማስተባበርና ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም