በካፋ ዞን የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በካፋ ዞን የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አሳድገዋል
ቦንጋ ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦በካፋ ዞን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን ሺሾእንዴ ወረዳ ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል ሞዴል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የወሺ ፏፏቴ የቱሪስት መዳረሻ፣ ሞዴል ጤና ኬላ እንዲሁም የኖባ ሽመሮ እና ወሺ ጊዳ የመንገድ መሰረተ ልማት ይጠቀሳሉ።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ እንደገለፁት፤ በዞኑ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አሳድገዋል።
ዛሬ የተመረቁ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም የዚሁ ማሳያዎች ናቸው ያሉት አቶ እንዳሻው፣ በዞኑ በዚህ ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በትምህርቱ ዘርፍ የሚስተዋለውን የጥራትና ውጤታማነት ችግር ለመፍታትም ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው አንዱ ተግባር ነው ያሉት አስተዳዳሪው በዚህም የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተሰራው ስራ ውጤት ማስመዝገቡን ነው የተናገሩት፡፡
የቱሪስት መዳረሻን በማልማት ረገድ ለወጣቶች ስራ ዕድል በመፍጠርና ቱሪስቶችን ለመሳብ በተደረገው ጥረት ዛሬ የተመረቀው የወሺ ፏፏቴ መዳረሻም የተደበቀውን እምቅ ሀብት አጉልቶ ያወጣ ነው ብለዋል።
የሺሾእንዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ ገብረማርያም በበኩላቸው፣ በወረዳው የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለሆኑ የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች መሰረተ ልማት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዛሬው እለት የተመረቁት መንገዶች አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ እንዲያወጣ እንዲሁም በፍጥነት የጤና አገልግሎትን እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብለዋል፡፡
የወረዳው ነዋሪዎችም ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው መንገድ ባለመኖሩ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣትም ሆነ ወደ ጤና ተቋማት ፈጥኖ ለመድረስ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ዛሬ የተመረቁት የትምህርት፣ የመንገድና የጤና ተቋማት ለበርካታ ዓመታት ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።