ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በለውጡ አመታት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ43ሺህ በላይ ደርሰዋል -ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በፊት ከ10ሺህ በታች የነበረው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በለውጡ አመታት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከ43ሺህ በላይ መድረሳቸውን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን መርቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የኦሮሚያ ክልልን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመደመር እሳቤን መሠረት በማድረግ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። 

በክልሉ ቡልቡላ እና ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የነቀምቴ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንባታው የተጀመረውን ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በዋቢነት አንስተዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ብቻ በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ባለሃብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት በሂደት ላይ እንደሚገኙ እና ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ደርሰዋል ብለዋል።
 
የክልሉ መንግሥት ቢሮክራሲን በመቀነስ፣ አሠራሮችን በማሳለጥ፣ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት እና ወጣቶች ክህሎት ይዘው የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን እየፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል። 

የዛሬው የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ምረቃም የዚሁ እንቅስቃሴ ውጤት አካል መሆኑን ነው የገለጹት። 

የግብርናው ዘርፍም ከተለመደው አሠራር ወጥቶ ወደ ኢንቨስትመንት እየተሸጋገረ መሆኑን ጠቁመው፣ በተያዘው መንገድ በቁርጠኝነት ከተሠራ የክልሉም ሆነ የሀገሪቱ ብልጽግና በአጭር ጊዜ እውን እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም