የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለቀጣናው ብልፅግና የላቀ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለቀጣናው ብልፅግና የላቀ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዲሁም ብልፅግናን ለማጎልበት የላቀ ሚና እንዳለው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ከመንከባከብ ባለፈ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ አደጋዎችን በጋራ ለመከላከል የአካባቢውን አገራት አብሮ የመልማት ዕቅድ ይዛ እየሠራች ስለመሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለጎረቤት አገራት በርካታ ችግኞችን ማበርከቷ ይታወቃል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ የተፈጥሮ መዛባቶችን ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አካባቢን ለመታደግ ታስቦ በከፍተኛ ሀገራዊ ቁርጠኝነት እየተተገበረ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ይህ ንቅናቄ በአገር ውስጥ ካስገኛቸው ሁለንተናዊ ጥቅሞች ባሻገር፣ ለጎረቤት አገራትና ለጠቅላላው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የምታከናውነው የተፈጥሮ ጥበቃ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለቀጣናው አገሮች የሚተርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በቀጣናው እንደ ጎርፍ፣ የበረሃ አንበጣ እና ድርቅ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሰዎችን መፈናቀልና ስደት ይፈጥራሉ፡፡
በዚህም ዜጎች ከአካባቢያቸው ችግሩ ወደ ሌለባቸው አካባቢዎችና ድንበሮችን አቋርጠው የሚሰደዱበትን ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን፤ ይህም በቀጣናው ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ይህንን ተግዳሮት ለመቋቋም በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጤቶችን እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታየው መደበኛ የዝናብ ሁኔታ ስኬት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር በቀጣናው የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር፣ ሰላምና ብልፅግናን ለማጎልበት የራሱ የሆነ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።
ይህንን የኢትዮጵያን መልካም ተሞክሮ በመረዳት እንደ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲ ያሉ የጎረቤት አገራት ተመሳሳይ አረንጓዴ ልማቶችን እየተከተሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ከዋና ዋና ዓላማዎቹ መካከል አንዱ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ልማት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሀሳብ በጽኑ እንደሚደግፈው ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲተገበር ቆይቷል።
በመርሀግብሩ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።
ይህ ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክት በኅብረተሰቡ ዘንድ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ በጎ ባህል እንዲዳብርና የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እንዲያድግ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በተለይም በችግኝ ማፍላት፣ በተከላና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።