ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የመንግስት አገልግሎት ተደራሽነትን ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል 

አገና፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት የህዝብ ተጠቃሚነት እና የመንግስት አገልግሎት ተደራሽነትን ያረጋገጡ የአሰራር ስርዓቶች በመዘርጋታቸው ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ አገና ከተማ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን የሚደግፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በወቅቱ ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ሳይፈቱ የቆዩ የልማትና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ የተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ በመጣቱ በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በከተማና ገጠር ልማት ሁለተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ውጤቶች ታይተዋል ብለዋል።

በተለይም በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተቀናጀና በዘላቂነት ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራትን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም የ"መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተለያዩ ከተሞች ወደ ስራ የገባው ይህ አሰራር፣ በርካታ ተቋማትን በአንድ ስፍራ በማቀፍ የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት የቆጠበ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ያጋጥም የነበረውን እንግልት በከፍተኛ ደረጃ አስቀርቷል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ መንግስት የህዳሴ ግድብን ባሳካው ልክ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችሉ የዲፕሎማቲክ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ታላቅ እቅድ በላቀ ተነሳሽነት ለማሳካት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ በበኩላቸው፤ በለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የመደመር መንግስት ለውጤት እንዲበቃ በማድረግ በኩል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ጀምሮ በማጠናቀቅ ረገድ ተምሳሌት መሆን ችሏል ነው ያሉት።

በክልሉ በገጠርና በከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስኬታማ በመሆኑ የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ማጎልበት እንደተቻለም አስረድተዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለውጤት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ይህም አገሪቱ ከተረጂነት ለመውጣት ለምታደርገው ጥረት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰልፉ ተሳታፊ የነበሩት አቶ መክብብ ገብረፃዲቅ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በውጤታማነት የመለሱ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በአንድነትና በመተባበር መለወጥ እንደሚቻል ያሳየ በመሆኑ ልማቱ እንዲቀጥል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም