በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ወላይታ ሶዶ ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።
በወላይታ ዞን የበሌ አዋሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የደረጃ ማሻሻያ ዕውቅና እና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ምረቃ መርሃ ግብር በበሌ አዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በየመዋቅሩ የጤና ተቋማትን በመገንባትና ባለሙያዎችን በመመደብ፣ ዜጎች የጤና አገልግሎትና መድኃኒት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የበሌ አዋሳ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃ ማሻሻልና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ምረቃ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህን አገልግሎቶች የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል።
አካባቢው ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሆስፒታሉ ደረጃ መሻሻልና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቱ መመረቅ የህዝቡን የዘመናት ችግር በዘላቂነት እንደሚቀርፍም ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል ስራዎችን ተግባራዊ በማድረጉ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የበሌ አዋሳ ሆስፒታል መደበኛ ህክምና፣ ድንገተኛ ህክምና እና የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎችንም የአገልግሎት ዘርፎች ያሟላ ሲሆን፣ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ከ70 በላይ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ ይህም ዜጎች መድኃኒትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ አስችሏል ነው ያሉት።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ በሁሉም መዋቅሮች የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የበሌ አዋሳ ከተማ ከንቲባ አባይነህ አጫ (ዶ/ር) በከተማው የጤና ተቋማት አቅም ማጎልበትን ጨምሮ በ75 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማህበረሰብ መድኃኒት ቤትና የሆስፒታሉ ደረጃ ማሻሻል ከእነዚህ መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ልማቱን ለማስቀጠል ከከተማው ነዋሪዎች ጋር የተጀመረው ቅንጅት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑት ወይዘሮ ርብቃ ጎዳና እና አቶ አስፋው አስራት በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ወላይታ ሶዶ እና ሌሎች ቦታዎች በመጓዝ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
የአሁኑ የሆስፒታሉ ደረጃ መሻሻል እንግልታቸውን እንዳስቀረላቸውና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቱ ደግሞ ደህንነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የተሻለ አማራጭ በመፍጠሩ መንግስትን አመስግነዋል።
በዚሁ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።