ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እስያገኘ ነው

ጂንካ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እ.ኤ.አ በ2030 ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ጥረት አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ከካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በጂንካ ከተማ አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ተወካይ አቶ ታምራት አሰፋ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና መከላከያ መድኃኒቶችን ተደራሽ በማድረግ የበሽታዎቹን ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ነው የገለጹት።

በዚህም ትኩረት የሚሹ የሀሩራማ በሽታዎች ተብለው ከተለዩት መካከል ትራኮማ፣ ወባ፣ ተላላፊ የዝሆኔ በሽታ እና የጊኒ ዎርም በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የጊኒ ዎርም በሽታን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፥ ባለፉት 15 ዓመታት በክልሉ ምንም ዓይነት የጊኒ ዎርም በሽታ አለመከሰቱን አረጋግጠዋል።

የዛሬው የምክክር መድረክ በቀጣይ በክልሉ የሀሩራማ በሽታዎችን ጨርሶ ለማጥፋት ለሚደረገው ርብርብ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ ምክትል ተጠሪ አቶ የማነ ቀጀላ በበኩላቸው፤ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት በሀገሪቱ የሀሩራማ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት የተያዘውን ብሔራዊ ግብ ለማሳካት ድርጅታቸው የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በተለይም ኦንኮሰርኪያስስ፣ ተላላፊ የዝሆኔ በሽታ እና የጊኒ ዎርም በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የሕክምና እና የመድኃኒት ድጋፍ በሀገሪቱ በሚገኙ ሰባት ክልሎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በካርተር ሴንተር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ታምራት በበኩላቸው፥ በክልሉ የኦንኮሰርኪያስስ እና የዝሆኔ በሽታን ለመከላከል መንስኤዎችን ከመለየት ጀምሮ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ድርጅቱ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከ974 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የዝሆኔ እና የኦንኮሰርኪያስስ በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎች 11 የአንጀት ጥገኛ ትላትሎችን መከላከል የሚያስችሉ መድኃኒቶች ተሰጥተዋል ብለዋል።

ለዚህም ተግባር የሚውል ከ5 ሚሊዮን በላይ የመድኃኒት እንክብል ለማኅበረሰቡ መሰራጨቱን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም