ቀጥታ፡

መንግስት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደው እርምጃ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በማሳለጥ በኩል ከፍተኛ ለውጥ አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደው እርምጃ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በማሳለጥ በኩል ከፍተኛ ለውጥ ማስገኘቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች እና የነዳጅ ማደያዎች ገለጹ፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ተከስቶ የነበረውን ችግር ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ ምርት አቅርቦት ላይ የተፈጠረው ክፍተት በሀገር ውስጥም የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል አስከትሎ የነበረ ቢሆንም፤ መንግሥት አቅርቦቱ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ደረጃ እንዲመለስ አድርጓል።

መንግሥት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደው እርምጃ የነበረውን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ተቋቁሞ ለማለፍ ያስቻለ ሲሆን፣ አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች የተረጋጋ፣ ቀልጣፋ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እንዲኖር አስችሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ሚያዝያ 21 ቀን 2018 . በወቅታዊ የዓለም የነዳጅ ሁኔታን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፣ የናፍጣ ነዳጅ አቅርቦት ከመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ መደረጉን መጥቀሳቸው ይታወቃል፡፡

ኢዜአ በመዲናዋ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎችና የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች፤ መንግሥት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደውን የማሻሻያ እርምጃ ተከትሎ በአቅርቦቱና በስርጭቱ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል።


 

አስተያየት ከሰጡ አሽከርካሪዎች መካከል አባይነህ ይሁኔ፤ ቀደም ሲል ከዓለም አቀፉ የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ በነበረው መስተጓጎል በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ ተፈትቶ ሁኔታው ወደ ቀድሞው በመመለሱ፣ በሁሉም ማደያዎች የሚፈልጉትን ያህል ነዳጅ ያለምንም እንግልት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ሌላኛው አሽከርካሪ ከድር ሁሴን በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ነዳጅ ለማግኘት እስከ አንድ ሳምንት ይወስድባቸው የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መፈታቱንና ያለምንም እንግልት ነዳጅ እያገኙ ማኅበረሰቡን በሚገባ እያገለገሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

በተመሳሳይ አሽከርካሪ ተፈሪ ዓለሙ እና ረታ ጂቢቲ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረው የነዳጅ እጥረትና የረጅም ሰዓት ወረፋ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በመቀረፉ፣ በአሁኑ ወቅት ያለምንም መስተጓጎል እየተስተናገዱ ይገኛሉ።


 

በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የነበረው ችግር በመወገዱ በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩንና መደበኛ ሥራቸውን በተሻለና ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የነዳጅ ማደያ ሱፐርቫይዘሮች በበኩላቸው ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ምክንያት ይፈጠር የነበረው የአቅርቦት ችግር በመቀረፉ ደንበኞቻቸውን ያለምንም እንግልት እያስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአቅርቦትና በስርጭት ላይ ችግር አለመኖሩን ጠቁመው ለማኅበረሰቡ ጥሩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በቡልጋሪያ አካባቢ ቶታል ማደያ ሱፐርቫይዘር ሰለሞን ገብረሕይወት እና በአሮጌው ቄራ አካባቢ ቶታል ማደያ ሱፐርቫይዘር ይርጋ ኪዳነ ማርያም ቀደም ሲል በነበረው እጥረት ምክንያት ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት እስከ አምስት ቀናት የሚደርስ ረጅም ሰልፍ ይጠብቁ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ችግሩ ሙሉ በሙሉ መቀረፉን አረጋግጠዋል።


 

በተመሳሳይ የሜክሲኮ አካባቢ የካምፖ አስመራ ነዳጅ ማደያ ሱፐርቫይዘር ጥበቡ በቀለ በበኩላቸው፤ መንግሥት ዓለም አቀፉን የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ ለማስተካከል የወሰደውን ቁርጠኛ እርምጃና የመጣውን ፈጣን አዎንታዊ ለውጥ አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ነዳጅ ለማደያቸው በአግባቡና በወቅቱ እየቀረበ መሆኑን ገልጸው እያገኙት ያለውን ምርትም ለተጠቃሚ አሽከርካሪዎች እያቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም