በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ የሚያሳድግ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ የሚያሳድግ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል
ወልቂጤ ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነታችንን ይበልጥ የሚያሳድግ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በጉራጌ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳ።
በዘንድሮው የመራጮች ምዝገባ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ ወስደው ቀኑን እየተጠባበቁ ሲሆን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ፖሊሲና ፕሮግራሞቻቸውን በምርጫ ቅስቀሳና በሚዲያ አማራጮች እያስተዋወቁ ነው።
ኢዜአ በጉራጌ ዞን ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች እንደገለጹት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠውን ትኩረትና ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድግ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
በዞኑ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ፕሬዝዳንት አቶ ዓብይ ጀማል በሰጡት አስተያየት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ከምዝገባ ሒደት ጀምሮ በተለያዩ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት የምርጫ ዓመታት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጓቸው ክርክሮች ላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነበር፤ በዚህ ዙር ግን ምርጫውን አካታች ለማድረግ የሚደረጉ አበረታች ጥረቶችን ታዝበናል ብለዋል።
በዞኑ በምርጫው ቅድመ ዝግጅት ወቅት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዓብይ፤ ከ23 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች ካርድ መውሰዳቸውንና 54 ታዛቢዎች ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ በመጠቀም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ነፃነት ፍቅሬ በበኩሉ፤ የምርጫ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው መደራጀታቸው ተሳትፏቸውን በእጅጉ እንዳሳደገው ገልጿል።
የተፈጠረውን ምቹ መደላድል በመጠቀም በምርጫው ዕለት ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አክሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን በሚያደርጉት የ"ይምረጡኝ" ክርክር ቅስቀሳ እና የማኒፌስቶ ማስተዋወቅ ላይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ዕቅዶች ሲንጸባረቁ መመልከታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ፈቀደ ባደታ ናቸው።
ምርጫው የሀገር ሰላምና የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን እንደሚመኙ ጠቅሰው፤ ለአካል ጉዳተኞች መብትና ተጠቃሚነት የሚቆረቆር ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የምርጫ ሂደት ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠው ትኩረት እንዳስደሰተው የተናገረው ወጣት ፈይሰል ሙደርም፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራን ፓርቲ ለመምረጥ ዝጁ መሆኑን አረጋግጧል።