ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የከተማ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ጎንደር፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የከተማ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ገለጹ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር በ550 የመኖሪያ ቤት ሕብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት መስሪያ ቦታ፣ የሳይትና የብሎክ ርክክብ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግሥት የቤት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂውን ወደ ተግባር በማውረድ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ አመራጮች የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሠራ ነው። 
 
መንግሥት የሕዝቡን አቅም በማስተባበርና ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

መሬት ውድና ውስን ሀብት በመሆኑ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትኩረት በመስጠት፣ ለኑሮ ምቹና ውብ የሆኑ ዘመናዊ ከተሞችን ለማስፋፋት የቤት ልማት ፖሊሲውን መሠረት ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው፤ በማኅበራት የተደራጁ ነዋሪዎች ፈጥነው ወደ ግንባታ መግባት እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እንደሚያሟላ ገልጸዋል።

ማኅበራቱ በገቡት ውል መሠረት ግንባታቸውን በፍጥነት መጀመር እንዳለባቸው ያሳሰቡት ምክትል ከንቲባው፤ መሬት አጥረው ለረጅም ዓመታት በሚያቆዩ ማኅበራት ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታዛዙ በጽሐ፤ በዛሬው ዕለት የቅየሳና የብሎክ ሥራ ተሠርቶላቸው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ ተጠቃሚ የሆኑት ከ13 ሺህ በላይ አባላትን ያቀፉ 550 የቤት ሥራ ማኅበራት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለእያንዳንዱ የማኅበር አባል 150 ካሬ ሜትር የግንባታ ቦታ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከተጠቃሚዎቹ መካከል የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች፣ በክብር የተመለሱ የሠራዊት አባላት፣ እንዲሁም ከስደት ተመላሾች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

የቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል አቶ ታደለ በላይ በሰጠው አስተያየት፤ ለረጅም ዓመታት በግለሰብ ቤት ኪራይ አስቸጋሪ ሕይወት ሲመራ መቆየቱን ገልጾ፣ አሁን ቦታውን በማግኘቱ ፈጥኖ በመገንባት የቤት ባለቤት ለመሆን መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ወጣት አማኑኤል ምሕረቱ በበኩሉ፤ የቤት መስሪያ ቦታ ዕድለኛ በመሆኑ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጿል።

በዚሁ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በቤት ሥራ ማኅበራት የተደራጁ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም